Sunday, August 21, 2011

ስልጠና

ስልጠና
መቼም በዚህ ክረምት ኢቴቪን እስኪበቃኝ ነው  የኮመኮምኳት፡፡ምናልባትም ለመጪዎቹ አስር ወራት ያህል የሚበቃኝን ያህል ብዙ ወሬ ሰምቼያለሁ፡፡ከተመላከትኳቸው ወይም ከሰማዋቸው ወሬዎች ዉስጥ የስልጠናዎች ነገር ግን አግራመትን ያጭርብኛል፡፡እስቲ እናንተም ስሙትና እንደፈለጋችሁ፡፡
ሰሞኑን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋም በመልካም ዉጤት የተመረቁና ለረዳት መምህርነት የተመለመሉ ምሩቃን በአዳማ(ናዝሬት) ከተማ ለ 2 ሳምንት የቆየ ሰልጠና ተካሂዷል፡፡ታዲያ በዚህ ጊዜ ነው አንዳንድ ምሩቃን በኢቴቪ መስኮት ብቅ እያሉ’’ስልጠናው እጅግ ጠቅሞናል፡በዩኒቨርሲቲ የተማርነውን ትምህርት እነዴት መተግበር እንዳለብን አውቀናል’’ስለዚህ ስልጠናው በህይወታችን እጅግ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል” ምናምን ብለው ነገሩን፡፡እኛም ሰማን መቼም ጆሮ ከመስማት አይሞላም አንዳለው መፃፉ፡፡
ስልጠና 2
የኢአዴግና አአጋር ፓርቲዎች ከፍተኛ አመራር አባላት ከትናንት በስቲያ ለሁለት ቀናት የተካሄደውን ስልጠና ሲጨርሱ አንዳንዶቹ እንዲህ አሉ”ስልጠናው የአፈፃፀም አቅማችንን በከፍተኛ ሁኔታ ቀይሮታል፣ምንም አንኳን ከፍተኛ አመራር ብንሆንም የአቅም ማነስ ችግር ነበረብን፡ከዚህ ስልጠና በኋላ ግን ሁኔታዎች ይቀየራሉ”ተባልን፡እሰይ ይሁን እንዳፋችሁ ያድርግላችሁ ወይም ያድሮግልን አልን፡፡
ስልጠና 3
የምንትስ ወረዳ አርሶ አደሮች ለአንድ ሳምንት የደረጉትን ስልጠና ሲያጠናቅቁ እንዲህ አሉ ተባለ”ያገኘነው ስልጠና እጅግ ጠቃሚ ነበር፡ባገኘነው ስልጠና መሰረት ምርታችንን በእጥፍ ማሳደግ እንችላለን፣የምግብ ዋስትና ችግራችንን እንቀርፋለን፡ ምናምን አሉ”እሰይ ያድርግልን ረሃብተኛ ከመባል ጥጋበኛ ለመባል ያብቃን አልን፡፡
መቋጫ፡-እኔ የመለው 3፣4፣5 እና ከዚያ በላይ ዓመት ዩኒቨርሲቲ የቆየ ተማሪ ለካ በ2 ሳምንት ስልጠና እንደዚህ ይቀየራል?ይሄንን ያህል አንድን ሰው ከመሰረቱ የሚቀይር ሶልጠና ሌሎቹ ምሩቃን አያስፈልጋቸውም?ይህ ነገር ለሁሉም ምሩቃን የሚዳረስበት መላ ቢዘየድ ምን ይመስላችኋል?ስልጠና በየቀበሌው ይብዛልን፡ተማሪዎቻችንም በሰልጠና ብቃታቸው ይጨምር፣ባለስልጣናቱም ችግራቸው ይቀርፍ፣ገበሬውም ምርቱ 30፡70 ና 100 ያፍራለት፡፡ስልጠና…ስልጠና… አሁንም ሰልጠና….

እኛ እና ቡሄ


እንኳን ለቡሄ በዓል አደረሳችሁ፣ አደረሰን!
አሁን እቤቴ ቁጭ ብዬ ትንንሽ የመንደራችን ልጆች መጥተናል ባመቱ እያሉ፣ሆያ ሆዬ ሆ!እያሉ መጡ ለካ ዛሬ ቡሄ ነው?ወይ ጉድ እናንተዬ ጊዜው እነ.ዴት ይሮጣል?እኛም እኮ ይሄው ልጆች ሲዘምሩ በትዝታ የልጅነት ጊዜያችንን  ማሰብ ቻልን፡፡ደስ አይልም?
ግን የቡሄ ግጥሞቻችን እጅግ ዘምነዋል አሊያም ዘቅጠዋል፡፡አንፃራዊ ነው ብዬ ነው፡፡ድሮ ድሮ የኔማ ጋሼ የሰጠኝ ሙክት መስከረም ጠባ እሱን ሳነክት ነበር፣ዘንድሮ ደግሞ እዛ ማዶ አንድ ጋሪ የኔማ አገሌ ጀት አብራሪ ሆኗል፡፡እነዲሁ ነገሩን ሳየው ትንሽ አግራሞት የሚያጭር ዓይነት ነው፡፡የቡሄ ግጥሞችን በማየት የሁለት ተውልዶችን ፍልስፍና ማወቅ የሚቻል መሰለኝ፡፡
የኛ ትውልድ ደሀ የቀን ሰራተኛ ቤት ሄዶ የኔማ እገሌ ባለታክሲ ምናምን ይላል፡፡ይሄ እንግዲህ ሰውዬው የሌለውን ሀብት ለአፍታም ቢሆን ያለው አነዲመስለው የሚያደርግ መልካም አጋጣሚ (ስድብም ሊሆን ይችላል የው እንደ ሰው ነው)ነው፡፡መግዛት ባይቻልም በቡሄ ጨፋሪ ልጆች አፍ ሀብታም መሆን ይቻላል ዓይነት ነው፡፡ሌላም አለ ከአራተኛ ክፍል ትምህርት ያቋረጠውን አባ ወራ ጀት አብራሪ ማለት ያው ተመሳሳይ ነገር ነው፡፡በእኔ እይታ ይሄ ነገር የኛ ትውልድ ፍልስፍና ባልተጨበጡ ኩነቶች ዙሪያ የሚያጠነጥን ዓይነት ነው፡፡
የድሮዎቹ ከእኛ ትንሽ የራቀ ይመስለኛል፡፡የኔማ እገሌ የሰጠኝ ሙክት መስከረም ጠባ እሱን ሳነክት፡፡ትንሽ ስነ ጥበባዊ ግነት የታከለበት እውነታ ይመስለኛል፡፡እንግዲህ ሰዎቹ ሪያሊስት አይነት ነገር ነበሩ ማለት ነው፡፡በእርግጥ ሌላም ልዩነት አለን፡የኛ ትውልድ ግጥሞች በቁሳዊ ነገሮች ላይ ያነጣጠረ ሲሆን የነሱ ግን ምግብ ነክ ግጠሞች ናቸው፡፡ይሄም እንግዲህ አንድ የሁለቱ ትውልዶች የህወት ፍልስፍና ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡
ሐሙስ 3፡20 ማታ
የቡሄ እለት

ፀሎትና ረብሻ

ሰሙኝማ ወዳጆቼ አሁን ይህቺን ቁርጥራጭሬ ልሞነጫጭር  የተነሳሁት በመከራ ያመጣሁት ዕንቅልፌ ሊወስደኝ ጫፍ ላይ ከደረሰ በኋላ ተነስቼ ነው፡፡አሁን ሰዓቱ ከለሊቱ 6፡48 ደቂቃ
ነዉ፡የመሞነጫጨር አባዜ ኖሮብኝ አይደለም በዚህ ውድቅት ለሊት ከሞቀ መኝታዬ  በመነሳት መብራት አብርቼ ጠረጴዛዬ ላይ የተሰየምኩት፡፡በገዛ ቤቴ፥መኝታዬ ላይ አትተኛም ተብዬ ነው መነሳቴ፡፡
እኔ የምለው እነኚህ የእምነት ተቋማት የሚገዟቸውን የድምፅ ማስጮሂያ መሳሪያዎች ከህንፃው ዉጭ የሚሰቅሏቸው ለምንድነው?ለምንስ በዚያ ስፍራ የሚካሄደውን የአምልኮ ወይም የትምህርት ስነ ስርዓት ፈልጎ በስፍራው ለተገኘው ምዕመን ብቻ ድምፁን መጥነው አይጠቀሙበትም?ይሄ በጣም የሚያሳዝነኝ እና የሚያስገርመኝ አይነኬ የሆነ የብዙዎቹ ቤተ ዕምነቶች የተለመደ የዘወትር ተግባራቸው ነው፡፡በእኔ ዕምነትነና ትዝብት መሰረት የትኛዉም የእምንት ተቋም ከዚህ ተግባር የፀዳ አይደለም፡፡አሁን እስቲ ትምህርቱን ፈልጎ በስፍራው የተገኘው ምዕመን እያለ ቤቱ የተኛው የዕምነቱ ተከታይ የሆነ ወይም ያለፀሆነዉ ሰው ለምን ይረበሻል?አሁን እኔንም የረበሸኝ በአካባቢዬ ያለ አንድ የቤተ እምነት ድምፅ ነው፡፡የቀኑንስ እሺ ይሁን ለምደነዋል፡አሁን በዚህ ውድቅት ለሊት በገዛ ቤቱ በሞቀ እንቅልፍ ላይ ያለ ሰው ለምን ይረበሻል?ያለ ዲምፅ መሳሪያስ ቢመለክ?እግዚአብሔር አይሰማ ይሆን?እባካችሁ ቢያንስ እስኪነጋ እንኳን የውጪውን መስመር አጥፉት?እኔም በመከራ የመጣ እንቅልፌን ለመመለስ አንድ 30 ደቂቃ ልገላበጥ፡፡
                                 ሐምሌ 30/2003 ዓ.ም

የስየ መፅሀፍ

“በመጀመሪያ ደረጃ ምርጫዉን ተከትሎ በተፈተሩት ሁኔታዎች ክፉኛ አዝኜያለሁ፡፡ኢህአዴግ እንደገና ዴሞክራሲን አልቀበልም አሻፈረኝ በማለቱ እትዮጵያ ሌላ ጥሩ አጋጣሚ ሲያመልጣት ስመለከት በጉዳዩ ላይ የእኔም እጅ ያለበት ያህል ነበር የጎደኝ፡፡’’
     ነፃነት እና ዳኝነት በኢትዮጵያ በ ስየ አብርሃ
አቶ ስዬ እዚህ ጋር ምን ለማለት እንደፈለጉ አልገባኝም፡፡የእድሜያቸውን እኩሌታ የኖሩበት ፓርቲ አሁን ባደረገው ነገር እኔ የለሁበትም ለማለት የፈለጉ ይመስላል፥ግን ማንም ፖለቲካን የሚያዉቅ ሰዉ እንደሚገምተው መቼም እንዲህ አይነት ለውጦች በአንድ ጀምበር አይከሰቱም፡፡ማለቴ ኢህአዴግ በባህሪው ይሄን ዓይነት ዝንባሌ ባይኖረው ኖሮ ለማለት ነው፡፡ይህ ከሆነ ደግሞ አቶ ስየንም የሚመለከት ጉዳይ ይሆናል ማለት ነው፡፡እሳቸው ይህን ያሉት በምርጫ 97 ዙሪያ ሲያወጉ ነው፡ያኔ ደግሞ እሳቸው ከፓርቲው ከተወገዱ ወይም ከለቀቁና ወህኒ ከወረዱ ገና 3 ዓመት ብቻ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
ሰባኪያን መፅፍ ቅዱስ ማንበባቸዉ በእርግጥ መልካም ነገር ነው፡ስራቸውም ስለሆነ፡፡ከመፀሐፍ ቅዱስ በተጓዳኝ ሌሎች መፅሐፍትን ማንበብ እንዲሁም የዓለምን ሁኔታ ማወቅ ደግሞ ብልህነትም አዋቂነትም ነው፡፡በርግጥ ሕገ መንግስቱ ምንም ቢልም ሰባኪያን እሱን በቤተ ክርስቲያን መድረክ ላይ መስበክ አይጠበቅባቸውም ደግሞም መፅሐፍ ቅዱስ የሕገ መንግስቱ ጭራ መሆን የለበትም ቤተ ክርስቲያንም የፖለቲካ መሸቀጫ አይደለችም ፡፡ነገር ግን ተገዙ ብቻ እያለ እንደ በቀቀን የሚበቀንን ሰባኪ ቤተ ክርስቲያን አያስፈልጋትም፡ለዚሀ ነው በመግቢያዬ ላይ የሚያነብ ሰባኪ ብልህ ነው ያልኩት፡፡ተገዙ እያለ የሚለፍፍ ሰባኪ ምዕመኑ ለማን እንደሚገዛ፤ እስከ የትስ እንደሚገዛ አብሮ ቢናገርም መልካም ነው፡፡መገዛት ማለት ቢጭኑት አህያ ቢጋልቡት ፈረስ አይነት ነገር ቢሆን ኖሮ ዛሬ እነሱ ቆመው የሚለፍፉበትን እድል ያገኙበት ከርስትና ራሱ በጠፋ ነበር፡እንገዛም ባሉ ቆራጦች ወንጌል እንደተስፋፋ ልብ ይሏል፡፡ሲሆን የቤተ ክርስቲያን መሪ የህዝብን መበደል፣ የመብት መጣስ ወዘተ አይቶ መንግስትን የሚወቅስና የሚኮንን መሆን ነበረበት(ይህን ዓይነቱን መሪ ሁልጊዜ እናፍቃለሁ) ካልቻለ ግን ዝም ማለት መልካም ነዉ፡፡ካላይ እንዳልኩት መፅሐፍ ቅዱስ መሪ እንጂ ጭራ አይደለም፡ ስለዚህ ተገዙ ያለው በእግዚአብሔር ለተሾሙ ባለ ስልጣናት መሆኑንም አበራችሁ ስበኩ፡፡በእግዚአብሔር የተሾመ መሪ ባህሪንም አብራችሁ ንገሩ፡፡መቼም እግዚአብሔር በአካል መጥቶ መሪ እንደማይሾም እሙን ነው፡ስለዚህ እኛን ይጠቀማል ማለት ነው፡እኛ ይሁንታ ያልሰጠነዉ መሪ ደግሞ መገዛታችን አይገባውም ማለት ነዉ፡

እንደገና

እንደገና የተሰኘዉን የኢቲቪ ዘጋቢ ፊልም ስመለከት አንድ ወጣት የላሊበላ ዉቅር አብያተ ክርስትያናት በር ላይ ቆሞ  በኢትዮጵያዊነቴ እኮራለሁ ሲል ሰማሁትና ዉስጤ ዝብርቅረቅ ያለ ስሜት ወረረኝ፡፡አሁን ላሊበላ፣አክሱም፣የፋሲል ቤተ መንግስት፣የሀረር ግንብን የሰሩ ዜጎች የኖሩባት ሀገር ዜጋ መሆን ምኑ ነዉ የሚያኮራዉ?አሁን አስቲ አባቴ ጀግና ነበር ብሎ ማዉራት ጉራ ከመንፋት ያለፈ ምን ፋይዳ አለዉ?የነሱ ልጅ ነኝ ስለሆንኩም ደግሞ እኮራለሁ ምን ይባላል?አሁን የዛን ዘመን ሰዎች ታሪክ እያወሩ በትዝታ መኖር ምን ለመፍጠር ነው? ባይሆን የኛ ታሪክ የወሎ ረሀብ፣ለ 30  ዓመታት የዘለቀዉ የእርስበርስ ፍጅት፣ወዘተ…ነዉ፡፡ምክንያቱም በዚህ ዘመን ስለኖርን በሱ ብናፍርም ወይም ደግሞ ብንኩራራም ያምርብናል።ለነገሩ እነኚህን ድንቅ ቅርሶች ትተዉልን ያለፉት ሰዎች በርግጥ ኢተዮጵያውያን ናቸዉን?እኔ ግን የሚመስለኝ ወይ ሰዎቹ ሰረተዉ ከሄዱ በኋላ ነዉ እኛን መሳዮቹ የኛ ወላጆች ወደዚህ አካባቢ የመጡት አሊያም የኛ ሰዎች ጥበብ አምሯቸዉ ከሌላ ፕላኔት አሊያም ከሆነ ቦታ አነዚህን የጥበብ ሰዎች አስመጥተዋቸዉ ይሆናል፡፡ለነገሩ ፕ/ር አነድሪያሰ ባሉት በጣም እስማማለሁ “ታሪካችኝ ይበዛብናል” ነበር ያሉት?እውነት አይመስላችሁም? ለዚህም ይመስለኛል ከማንነታችን በላይ የገዘፈ ታሪክ እያወራን፡እነእንቶኔን እኮ ድሮ እንበልጠቸዉ ነበር ቅብርጥሴ እያልን የቀረነዉ።አሁን ደግሞ አዲሷ አገር ደቡብ ሱዳን ነገ ስትበልጠን እንደለመደብን ድሮ እንበልጣት ነበር እንል ይሆን?መቼ ይሆን በሞቱ ሰዎች ታሪክ መኩራራቱን ትተን እኛ በሰራነዉና በምንሰራዉ ማፈር የምንጀምረዉ?ይሄን የምለዉ ያለንበትን ማወቁ ለለዉጥ ጅማሬዉ ነው ብዬ ነዉ፡እንደዚያ ብናደርግ ታሪካቸውን ለ ዉጭ ሀገር ሰው እያሳየን የምንኮራባቸዉ የዚያ ዘመን ሰዎች አፅምም በእፎይታ የሚያርፍ ይመስለኛል።

ኢንተርኔትና ዩኒቨርሲቲ

ዩኒቨርሲቲ የሚለውን የእንግሊዘኛ ቃል መዝገበ ቃላቶች ጥራት ያለው ከፍተኛ ትምህርት መጥኛ ተቋም በማለት ይፈቱታል፡፡በሌላም በኩል ቃሉ የሁለት ጥምር ቃላት( univer +sality)(sity) ውጤት እንደሆነ የሚገልፁም አ
ሉ፡፡ይህም እነኚህ ተቋማት ዓለም ዓቀፋዊ ጥራት ያለዉ ትምህርት፡የኑሮ ዘይቤ፡አስተሳሰብ፡እና ስብእና የሚገበይባቸው ተቋማት ሰለመሆናቸው አመላካች ነው፡፡በእርግጥም ናቸዉ፡፡በአገራችን እነዚህ ተቋማት ይህንን ባህሪያቸውን ይዘው ይሁን አሊያም ስማቸውን ብቻ ቁጥራቸው 31 መድረሱን ሰምተናል፡፡እስቲ አዳዲሶቹን እንተዋቸውና ነባሮቹ ምን ያህል ስማቸውን እንደወከሉ እንመልከት፡፡መቼም አንድ ዩኒቨርሲቲ ደረጃውን የጠበቀ ነው እንዲባል ሊያካትታቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ፡ከነዚህም ውስጥ፡ ደረጃውን የጠበቀ ቤተ መፃህፍት( ይሄ የተሟላ የኢነተርኔት አገልግሎትንም ይጨምራል)፣ብቁ መምህራን፣የመማሪያና የመኖሪያ ህንፃዎች ወዘተርፈ፡፡ይህን ካልኩ ዘንዳ የዛሬ ወሬዬን ከላይ በቅንፍ የተሟላ ብዬ ከገለፅኩት የኢነተርኔት አቅርቦት ላይ ላተኩር፡፡በነገራችን ላይ ዩኒቨርሲቲዎች ምዕሉ በኲሉህ የሆነ ተማሪ ለማፍራት በዚህ ባለንበት ክፍለ ዘመን በቂ የሆነ የኢንተርኔት አገልግሎት ሊኖራቸው ግድ ነው፡፡እርግጥ ነው ሁሉም ባይሆኑም አብዛኞቹ ነባር ተቆማት አገልግሎቱ አላቸው፡ጥራቱና ስርጭቱ ቢለያይም ማለቴ ነው፡፡ከእነዚሀ መሰል ተቋማት አንዱ ደግሞ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ከነበረው የኢነተርኔት አገልግሎት አንፃር ሲታይ ጥሩ ስርጭት አለው፡፡የጭን ኮምፒተር ያላቸው ተማሪዎችም የገመድ አልባ አገልግሎት ያገኛሉ፡፡ይሄም ሆኖ ተቋሙ ተፈላጊና ተነባቢ ሳይቶችን በመገደብም(block በማድረግ) አይታማም፡፡ይሄ ልክ ፓስታ ሰጥቶ ሹካ እንደመከልከል ዓይነት ነው፡፡አንዳንድ የዳያስፖራ ብሎጎች እዚህ አገር አገልግሎት እንደማይሰጡ ይታወቃል ነግር ግን ፌስ ቡክ በአገራችን የተገደበ ሳይት አይደለም፡፡ዩኒቨርሲቲዎች ግን ቢቻል የታገዱትን ብሎጎች ሊያስነብቡን ይገባ ነበር፡ምክንያቱም እነኚህ ተቋማት በነፃነት የሚያስብ ዜጋ ማፍሪያ ቦተዎች ነቸዋ፡፡እነሱ ግን እኛ ከምንሰጣችሁ ውጪ ማንባብም ሆነ ማየት ያደነቁራችኋል የሚሉ ይመስላሉ፡፡ለምሳሌ በአዲስ አበባ ዩኒቨረሲቲ ፌስ ቡክን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ሳርቶችን መጎብኘት አይቻልም፡፡እነኚህ እንግዲህ ሌላው ማህበረሰብ እንደልቡ የሚጐበኛቸው ሳይቶች ናቸው፡ታዲያ ይሄኔ ምነው ተማሪ ባልሆንኩ አያሰኝም?ለመሆኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ይሄን የሚያደርገው ለምን ይሆን?በራሱ የሚተማመንና ነፃ የሆነ ዜጋ ማፍራትስ አይመለከተው ይሆን’ዴ?በመቀሌ ዩኒቨርሲቲም ተመሳሳይ ነው፡፡እነኚህ ተቋማት ታዲያ  ዩኒቨርሲቲ የሚያሰኛቸውን አንድ ዋና ነገር አላጡም ትላላችሁ?እያስተማሩ በሌላ በኩል ተማሪን ከመረጃ መገደብ ምን ይሉታል?የመረጃ ነፃነትን የማያከብር ተቋም ዩኒቨርሲቲ ወይስ ዩኒቨርሳል ዕጢ?
ረቡዕ ነሀሴ 4/2003  1፡51 ማታ
    ቤቴ