ጊዜዉ በ 1997 ዓ.ም ያ የኛ ዘመን ታሪካዊ ምርጫ ሊደረግ የተቃረበበት ሚያዚያ አጋማሽ አካባቢ ይመስለኛል፡፡ አንድ ቀን አመሻሽ ላይ እቤቴ ሆኜ በትንሽዬ ሬዲዮኔ በመካከለኛ ሞገድ የሚተላለፈዉን የሬዲዮ ፋና ዝግጅት በማድመጥ ላይ ነኝ፡፡በነገራችን ላይ ጣቢያዉ አንድ ለእናቱ ሆኖ የቀረዉን ምርጫ በማስመልከት፡ለጠቅላይ ሚንስትሩ የሚቀርብ ጥያቄ ከአድማጮች ቀደም ብሎ አሰባስቦ ነበር፡እናም ዛሬ አቶ መለስ መልስ የሚሰጡበት ወይም ቃለ ምልልሱ የሚደመጥበት ቀን ነበር፡፡መቼም የአንድ አገር መሪ በተለይም ምርጫን የሚያህል ጉዳይ ልታካሂድ መንገድ ለይ ያለች ሀገር፤የሚያደርጉትን ቃለ ምልልስ ማድመጥ ምን ያህል ጆሮ ገብ ወሬ ሊሆን እንደሚችል መቼም የምታዉቁት ነዉ፡፡እኔም በወቅቱ ሀገራችን ወፘ እንደገባ እረጉዝ ግንቦት ሰባትን ትጠብቅ ነበርና (ምርጫው የተደረገው ግንቦት 7 ስለ ነበር ነው፤ዘንድሮ ግነቦት 7 ሌላ ትርጉም ስላለው) የጠ/ሚንስተሩን ቃለ መጠይቅ ሁሉንም የስሜት ህዋሳቶቼን ጆሮ አድርጌ ሰማሁት፡፡መቼም በወቅቱ የነበረውን ከፍተኛ የሆነ መነሳሳት ለማን እናገራለሁ?(political revival) ምናልባትም ያ ወቅት የፖለቲካችን ህዳሴ ሳይሆን አይቀርም፡፡ህዳሴ እንደዚህ ነው እንዴ?የምትሉ ከሆነ ልክ ብላችኋል፡ምን አልባት አያያዙን ሳንችልበት ቀርተን ይሆናላ፡፡እናም ወደ ጉዳያችን ስነመለስ ሰወዬው እየተናገሩ ነው፡፡የተለያዩ ጥቄዎች ተጠይቀዋል፡፡ለምሳሌ፡-ስለ ባንዲራ፣የባህር በር፣የአከክሱም ሀውልት እና ወላይታ፤ይሄን ጥያቄ በደንብ ለመግለጽ፡ በአንድ ወቅት አቶ መለስ አምልጦአቸዉ ይሁን አስበውበት እኔ አላውቅም፡፡ ብቻ በሆነ ንግግራቸው መሀል የአክሱም ሀውልት ለወላይታው ምኑ ነው ብለው ነበር አሉ፡፡ለሉአላዊነቷ ደሙን ሳይሰስት ያፈሰሰ፣ስጋውን የቆረሰ፣አጥንቱን የከሰከሰ፣ታሪክሽ ታሪኬ፣መዋረድሽ ውርደቴ፣ክብርሽ ክብሬ፣ካንቺ የተለየ ማንነት የለኝም ብሎ በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራውን የወላይታ ህዝብ፡የአከሱም ተሪክ ላንተ ምንህ ነው፡መባሉ እንዳስቆጨው አቶ መለስ አልገባቸውም ወይም እነዲገባቸው አልፈለጉም፡፡እናም በዚህ ቀን ይህ ጥያቄ ቀረበላቸው፤ምን ማለት እነደፈለጉም ዋጋ ቢያስከፍላቸውም፡ለማስተባበል ሞከሩ፡፡በዚሁ ጊዜ የተጠየቁትና መልስ የሰጡበት ጉዳይ፡ዘንድሮም የሚጠየቁት መቼ ስልጣን ይለቃሉ የሚለው ጥያቄ ነበር፡፡በእርግጥ ይህን ጥያቄ ሲመልሱ፡ኢትዮጵያን ከጃፓን ጋር በማነጻጸር ጃፓን ላለፉት 50 ዓመታት በአንድ ፓርቲ እነደምትመራና ይሄም ከእድገቷ ጋር ያለውን ትስስር በማብራራት፡ፓርቲያቸው ገና 15 ዓመት ብቻ እነደገዛና ለሚቀጥለው ግማሽ ምዕተ ዓመት ኢህአዴግ ቢያስተዳድር ወይም ቢገዛ(የፈለጋችሁትን በሉት) ሀገራችን አንደ ጃፓን ትሆናለች የሚል ዓይነት አንድምታ ያለው ነገር ተናገሩ፡፡እኔ ግን ዘንድሮ ይሄ የአቶ መለስ ንግግር ትዝ ብሎኝ፡እኚህ ሰውዬ የተናገሩትን ነገር የሰይጣን ጆሮ አይስማው አልኩኝ፡፡ወድጄ አይደለም ለእሳቸው ለራሳቸው ብዬ ነው፡፡ለእኛማ እነደ ጃፓን ብንሆን አንጠላም፡ግን…?እሰቲ ጃፓን ምን ሆነች?እንይ.ጃፓን ከ 2007 ወዲህ እነሆ 6ኛውን ጠ/ሚንስትሯን ሾመች፡ምን ጉድ ነው ጉልቻ ቢቀያየር ምን ያጣፍጥ ይመስል ጠ/ሚነስትር መቀያየር ምን ይረባል?ምናምን አሉ ወዳጄ?ሀገሩ ጃፓን ነው፡፡ ምን ይደረግ፡፡የተፈጥሮ አደጋ ሲከሰት የወሰድከው እረምጃ በቂ አይደለም ተብሎ ከስልጣን ያስባርራል-በጃፓን፡፡ግምገማ፣ሂሰ አውርዶ በንስሃ ራስን ማደስ ምናምን የለ፣በቃ ውረድ ነው፡፡አኛ ታዲያ፡ምስኪኖቹ ኢትዮጵያውያን፡ያሉን አንድ እሳቸው ናቸው፡ማን እሳቸውን ይተካልን ነበር? ማንን እንቀያይር ነበር-አነደ ጃፓን ብንሆን?እሰቲ አስቡት፡ከ 97 ወዲህ እንኳን ስንቴ፡ስንት ሚሊዮኖች ተራቡ?ታዲያ አነደጃፓን ጠ/ሚንስትሩ በተወቀሱ ቁጥር ስልጣን ቢለቁ ኖሮ ማን ይመራን ነበር? እሳቸውስ ማንን ይመሩ ነበር? (ይገዙ ነበር አላልኩም)በእርግጥ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከስልጣኑ የወረደ ባለ ስልጣን እንደ እባብ አፈር ቅሞ ዳግም ህይወቱን የሚያድስባት ናት፡ቢሆንም ግን መንግስታችንን አንደ ጃፓን አያድርግብን፡፡የምር ግን አቶ መለስ እንደ ጃፓን መሆን ለምን ይመኛሉ?¡